በአቶ ያንግ ያሊን የዩናን ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር የተመራ የቻይና ዩናን ግዛት ልዑክ ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮች ጋር በቡና ንግድ ትስስር ላይ ውይይት አካሄዱ፡፡
ልዑኮቹን ተቀብለው ያነጋገሩት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ ለልዑኩ አጭር ገለጻ አድርገዋል። በገለጻቸውም ቀደም ሲል የተለያዩ የቻይና ልዑኮች ወደ ባለስልጣኑ በመምጣት ውይይቶች እንደተካሄዱ ተናግረዋል፡፡ በመቀጠልም ባለስልጣኑ የሀገሪቱን የቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ምርትና ግብይት ለማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም እንደሆነ ገልጸው ለሰብሎቹ ምርታማነት የተለያዩ የቴክኖሎጂ እና ስልጠና ግብአቶች ለአርሷደሩ እየሰጠ ያለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 90 በመቶ የቡና ምርት የሚገኘው ከአርሷደር ጓሮ ስለሆነ ባለስልጣኑ በቀጥታ ከአርሷደሩ ጋ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ አርሷደሩ በቀጥታ ቡና ኤክስፖርት እንዲያደርግ የሚፈቅድ መመሪያ እንደወጣና አርሷደሮቹ በቀጥታ ቡና ወደውጪ መላክ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ድረስ በባህላዊ መንገድ ቡና በጥላ ዛፍ ስር እየተመረተ እንደሆነና በቀጣይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ያለጥላ ዛፍ ቡና በማምረት አመራረቱን ለማዘመን ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ከምርት በኋላ ያለውን ሁኔታ ጋር በተያያዘ የባለስልጣኑ ተግባርና ኃላፊነቱን ሲናገሩም ባለስልጣኑ የምርት ጥራት መቆጣጠር፣ ስታንዳርዳይዜሽን እና ሰርቲፊኬሽን ላይ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ በምርቶቹ ገበያ ማስፋፋት ላይ እንደሚንቀሳቀስም ገልጸው ይህንንም ከዳር ለማድረስ በተለያዩ ሀገራት ምርቶቹን የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ እንዳለ አውስተዋል፡፡ በዚህም የተለያዩ የቻይና ካምፓኒዎች ወደባለስልጣኑ በመምጣት የቡና ግብይት ፍላጎቶቻቸውን እንደገለጹ ጠቅሰዋል፣ በባለስልጣኑ የተገኘውም ልዑክ ስለጎበኛቸውም ደስታቸውን ገልጸው እንኳን ደህና መጣቹ ብለዋል፡፡
የቻይናው ልዑክ መሪም አቶ ያንግ ያሊን ስለመጡበት ጉዳይ አጠር ያለ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በፊት ከመጡ የቻይና አካላት ጋር ባለስልጣኑ እንደመነጋገሩ አስቀድሞ ግንኙነት መጀመሩ ጠቅሰው ይህ ልዑክ እንደማንኛው ከዚህ ቀደም እንደመጡት ልዑካን ሁሉ የንግድ ትስስርንና አጠቃላይ የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የመጡበት ዩናን ግዛት 400 ሺ ስክዌር ኪ/ሜ ስፋ እንዳለውና 47 ሚሊየን ሕዝብ የሚኖርበት እንደሆነ ከገለጹ በኋላም ሻይ እና ቡና እንደባህል ሆኖ የሚጠጣበት ግዛት እንደሆነ ገልጸው አካባቢው በአየር ንብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚመሳሰል በዚህም አረቢካ ቡና የሚመረትበት አካባቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአካቢው የቡና ምርት የቻይናን 80 በመቶ የቡና ምርት የሚመረትበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት መስራቱ ይጠቅመናል በማለትም ነው እዚህ የተገኘነው ብለዋል፡፡
ልዑኩ ገለጻቸውን ካቀረበ በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ለተነሱት ጥየቄዎች ዶ/ር አዱኛ ደበላ በቂ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከተነሱት ጥየቄዎች አንዱ የቡና ጥራት ቁጥጥር የሚመለከት ሲሆን ለዚህም ዋና ዳይሬክተሩ ምላሽ ሲሰጡ የቡና ጥራት የሚመረምር ዲፓርትመንት እንዳለ፤ ቡናው እዚህ ከመድረሱ በፊት ጥራት ያለው ቡና እንዲመረት በስልጠናና ሌሎች እግብአቶች በማገዝ አርሷደሩ ጥራት ያለው ቡና እንዲያመርት አስቀድሞ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ ከአርሷደሮቹ ባሻገር በቡና ሰንሰለት ውስጥ ላሉ እንደ አቅራቢና ላኪ ያሉ አካላትንም ጥራት ያለው ቡና አዘገጃጀት ላይ ስልጠና እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ማዕከላት በቡና አምራች አካባቢዎች እንደተከፈቱ፣ ወደ 20 የሚጠጉ የቡና ጥራት ምርመራ ላብራቶሪዎች እንዳሉና በእነሱ በኩል የቡና ጥራት እንደሚመረመር ገልጸዋል፡፡ በመንግስት ተቋም ስር ብቻ ሳይሆን እያንዳንዳቸው የቡና ላኪ ድርጅቶችም የራሳቸው የቡና ጥራት መመርመሪያ ላብራቶሪ አላቸው ብለዋል፡፡ ማንኛውም ወደውጪ የሚላከው ቡና በእነዚህ ላብራቶሪዎች በኩል ተመርምሮና ጥራቱ ተረጋግጦ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከ ደረጃ 1-5 ጥራት ያላቸው ቡና እንደሚላኩ ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህ ቡናዎች ውጪ ቡና እንደሚሸጥ ለተነሳው ጥያቄም ሲመልሱ ደንብና መመሪያ ከእነዚህ ውጪ መሸጥ እንደማይፈቅድ ገልጸው የቡና ፓርችመንትና የቡና ቅጠል ግዥ ጥያቄ ግን ከተለያዩ ደንበኞች እንደሚቀርብ ጠቅሰዋል፡፡
ዶ/ር አዱኛ ደበላ ከልዑኩ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡ በኋላም ከሳቸው በኩል ያለውን ፍላጎት ሲያቀርቡም ከቡና ባሻገር በሻሂ ምርት ግብይት ዙሪያም ከቻይና ጋር መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ቻይና በሻይ ረገድ ከፍተኛ ልምድ ያላት እንደመሆኑ በልዩ ልዩ መልኩ ቻይና እገዛ ብታደርግ መልካም ነው ሲሉ ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ እስካሁንም ሻይ ወደ ሞምባሳ ብቻ እየተላከ እንደሆነ ገልጸው የሻይ ምርት 3 ሺ ሄክታር ላይ ብቻ እየተመረተ እንደሆነ፤ በቀጣይም ወደ 30 ሺ ሄክታር ለማስፋፋት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከቤት ውስጥ ውይይቱም በኋላ የባለስልጣኑን የቡና ማሰልጠኛ ማዕከል የጎበኙ ሲሆን በውይይት ወቅት ልዑካኑ ስለቡና ጥራት ምርመራ ሂደት ላነሱት ጥያቄ ከቡና ቅምሻ ስልጠናው ጋር በተያያዘ ምላሽ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
አሸናፊ ጌታሁን እንደዘገበው
.





Comment (1)
Johny November 19, 2018 at 12:44 pm
Your superannuation may be paid out to your beneficiaries if pass away unexpectedly. Ensure you know who your nominated beneficiaries are and exactly who receives those payments